የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅን ያሻሻለው አዋጅ ቁ. 1307/2016 ምን ምን ለውጦች ይዟል?

በዜጎች ላይ በዘፈቀደ የሚፈፀሙ የአስተዳደር በደሎች የሚቆሙበትን ወይም የሚታረሙበትን ቀልጣፋ አሰራር በመዘርጋት ለመልካም አስተዳደር መሰረት መጣልን አላማ አድርጎ በአዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የተቋሙን ተግባርና ኃላፊነት በማስፋት በግል ድርጅቶች የሚፈፀሙ የአስተዳደር በደሎችን አቤቱታ መቀበል እና ምርመራ ማካሄድ አስፈላጊነቱ ስለታመነበት በስራ ላይ የቆየውን የተቋሙን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 1142/2011 ለማሻሻል አዋጅ ቁጥር 1307/2016 ፀድቋል።

 ይህ ማሻሻያ አዋጅ የያዛቸው ዋና ዋና ለውጦች ተቋሙ በግል ድርጅቶች ጭምር ስልጣን እንዲኖረው ከማድረግ ጋር የተያያዙ ሲሆኑ እነሱም፤

  1. ስልጣን ባለው አካል የወጣ እና በስራ ላይ ያለ ሕግን በመፃረር በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚፈፀሙ ድርጊቶች ወይም የሚሰጥ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ የአስተዳደር በደል ተደርገው የሚቆጠሩ መሆኑን አካቷል።
  2. በግል ድርጅቶች ውስጥ የአስተዳደር ወይም የአስተዳደር ነክ አገልግሎት የሚሰጥ አካል ተመርማሪ አካላት በሚለው ትርጓሜ ውስጥ እንዲካተት አድርጓል።
  3. የግል ድርጅት ሲባል በንግድ ህጉ የተገለፁት የንግድ ማሕበር አይነቶች ሆነው የማምረት፣ የማከፋፈል፣ የአገልግሎት እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ተግባሮችንና ከእነዚሁ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በንግድ መልክ የሚሰሩትን ሁሉ እንዲያጠቃልል አድርጓል።
  4. አዋጁ በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት እና በግል ድርጅቶች በሚፈፀሙ የአስተዳደር በደሎችና ባለሥልጣኖች እና ኃላፊዎች ላይ ተፈፃሚነት እንደሚኖረው ደንግጓል።
  5. ለተቋሙ በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚፈፀሙ የአስተዳደር በደል አቤቱታዎችን የመቀበል እና ምርመራ የማካሄድ ስልጣን እና ኃላፊነት ሰጥቷል።

ተቋሙ በፍርድ ቤቶች ወይም በሕግ የመዳኘት ስልጣን በተሰጣቸው አካላት በመታየት ላይ ያሉ ወይም ታይተው የመጨረሻ ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮችን የመቀበልም ሆነ የመመርመር ስልጣን የሌለው መሆኑ፣ በስልጣኑ ስር በሚወድቁት ጉዳዮችም ቢሆን የመጨረሻ ውሳኔው ምክረ ሃሳብ ከማቅረብ ያልዘለለ፣ አስተዳደራዊ፣ የፍታብሔር ወይም የወንጀል ተጠያቂነት የመፍጠር አይነተኛ ስልጣን የሌለው መሆኑ ሊኖረው የሚችለውን አበርክቶ በእጅጉ የሚገድብ ቢሆንም ዜጎች ደረሰብን የሚሉትን አስተዳደራዊ በደል የግል ተቋማትን ጨምሮ ብሶታቸውን ለማሰማት ተጨማሪ የመፍትሔ አማራጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ግን ጥርጥር የለውም።