የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ደንብ ዳሰሳ

የፈንዱ ምንነት

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 482/2013 የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድህን ፈንድ አስተዳደርን አቋቋሙዋል፡፡ የዚህ ደንብ ዋና አላማ የፋይናንስ ዘርፉ የተረጋጋ ለማድረግ እና ለገንዘብ አስቀማጮች ጥበቃ ለማድረግ ነው፡፡ የፈንድ አስተዳደሩ ተጠሪነት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሲሆን የብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ የገንዘብ ሚኒስትር፣ ምክትል ገዥ፣ የባንኪንግ ቁጥጥር ዲይሬክተር እና የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ቁጥጥር ዲይሬክተር የቦርደ ቋሚ አባለት እና ሁለት ከባንኮች እና ከአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ማህበራት የሚወከሉ አጠቃላይ ሰባት የቦርድ አባለት ይኖሩታል፡፡ በደንቡ አንቀጽ 2(11 እና 19) እና አንቀጽ 16(1) መሰረት ሁሉም ፋይናንስ ተቋማት ማለትም በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጠው እና ከህዝብ ተቀማጭ ገንዘብ የሚሰበስብ የንግድ ባንክ እና አነስተኛ ፋይናንስ ተቋም የዚህ ፈንድ አባል የሚሆኑ ሲሆን ደንቡ ሥራ ላይ ከዋለ በ30 ቀናት ውስጥ ፈንዱ ጋር የአባልነት ውል በመዋዋል ከፈንዱ የሚወሰነውን መነሻ የአረቦን ክፍያ ይፈፅማሉ፡፡

  • የፈንዱ ሥልጣን እና ተግባር (አንቀጽ 6)
  • መነሻና ዓመታዊ የአረቦኖች መጠን መወሰን፣
  • በመድን የተሸፈኑ ተቀማጭ ገንዘብ የሽፋን ጣሪያ መወሰን፣ አስፈላጊ ሲሆን ማሻሻል፣
  • ለፈንዱ የሚቀርቡ የካሣ ክፍያ ጥያቄዎችን መገምገም፣
  • የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥመዉ፣ ከመንግሥት እና/ወይም ከሌሎች ምንጮች ብድር የሚያገኝበትን ፖሊሲ ማዉጣት፣
  • ለገንዘብ አስቀማጮች የፈጸማቸዉን ክፍያዎች ከወደቁ የፋይናንስ ተቋማት የንብረት ማጣራት ተመላሽ ማድረግ
  • የፈንዱን ሀብት ኢንቨስት ማድረግና ማስተዳደር፣
  • ከዓለም አቀፍ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ሰጪ አካላት ጋር መተባበር፣ እና ሌሎች
  • ስለመድን ክስተት እና መድኑ የሚሸፈኑ ተቀማጭ ገንዘቦች
  • በዚህ ደንብ አንቀጽ 21 መሰረት የመድን ክስተት (Insurance Event) የሚፈጠረው የወደቁ የፋይናንስ ተቋማት የሥራ ፈቃድ የተዘረዘ መሆኑ በብሔራዊ ባንክ ሲታወጅ እና በዚህ ደንብ መሰረት ፈንዱ በመድን የተሸፈነውን የተቋሙን ተቀማጭ ገንዘብ ለመሸፈን ሲወስን ነው፡፡
  • በመድን የሚሸፈነው የገንዘብ መጠን
  • በፋይናንስ ተቋሙ በተለያዩ ሂሳቦች ውስጥ የተቀመጠ የገንዘብ መጠን እና የመድን ክስተቱ እስከተፈጠረበት ቀን ያለው ወለድ፣
  • ተቀማጭ ገንዘቦቹ የተቀመጡት በዉጭ ምንዛሪ ከሆነ የፋይናንስ ተቋሙ የመድን ክስተት በተፈጠረበት ዕለት የሚኖረውን የመግዣ የምንዛሪ ተመን
  • የፈንዱ አባልነት እና ከአባልነት ስለመሰናበት
  • የትኛዉም የፋይናንስ ተቋም የፈንዱ አባል ይሆናል፡፡
  • ደንቡ ከወጣ በኋላ የሚመሠረት የፋይናንስ ተቋም የፈንደ አባልነት ተቋሙ የሥራ ፈቃድ ካገኘበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡
  • የፈንዱ አባል የነበረው የፋይናንስ ተቋም ከአባልነት የሚሰናበተው፡-
  • የተሰጠዉ የሥራ ፈቃድ በብሔራዊ ባንክ ተመላሽ ከተደረገ፣ ከተሰረዘ፣ ወይም ከተነጠቀ፤
  • በፋይናንስ ተቋሙ ላይ የመፍረስ ውሳኔ ከተላለፈበት፤
  • የአባል የፋይናንስ ተቋም ተቀማጭ ገንዘቦች ሙሉ በሙሉ ወደ ሌላ የፋይናንስ ተቋም ከተላለፈ፤
  • በአባል የፋይናንስ ተቋም በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የመፍረስ ጥያቄ መሠረት የንብረት አጣሪ ከተሾመ፤
  • አባል የፋይናንስ ተቋም ከሌላ የፋይናንስ ተቋም ጋር ሲቀላቀል ወይም ሲዋሃድ ነው፡፡